Response to Removal of the name Ethiopia from the Bible

ኢትዮጵያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ  የማውጣት አሳፋሪ ፕሮጄክት

በቅርቡ በጀርመን ሐገር የሚኖር በንቲ ኦጁሉ ቴሶ የተባለ ሰው ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማውጣት ‹‹ጥናት›› አድጎ በዚሁ ጥናት ዶክትሬቱን እንደተቀበለ ተናግሯል፡፡ ይህ ሰው “ኦፕራይድ” ለሚባል ድረ-ገጽ ጋዜጠኛ የሰጠውን ቃለ ምልልስ የአማርኛ ትርጉም አነበብኩት፡፡ ዶ/ር በንቲ የጀርመን ኢቫንጀሊካን ቤተክርስቲያን ፓስተር ሲሆን በቅርቡ የዶክትርና ትምህርቱን የጨረሰው ኢትዮጵያ ስሟ ከመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰረዝ ባደረገው ‹‹ጥናት›› እንደሆነ በቃለ  ምልልሱ ተናግሯል፡፡ ቃለ ምልልሱን አንብቤ ጉዳዩ ዝም የሚያሰኝ ስላልሆነ ለዶ/ር በንቲ ቴሶ ‹‹ጥናት›› የድርሻዬን ምላሽ ለመስጠት ተገድጃለሁ። ኢትዮጵያዊነት የግለሰብ ወይ የአንድ ቡድን ውሳኔ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ክብር ስለሆነ ሌሎች በጉዳዩ የሚመለከታቸውንም ወገኖች ምላሽ ቢሰጡበት መልካም ነው እላለሁ፡፡

ከጅማሬው አንባቢዎቼን ማሳሰብ የምወደው፣ እኔ ዶክትሬቴን የሰራሁት በባዮ-ኬሚስትሪ እንጂ በታሪክ ምርምር አይደለም፡፡ ዶ/ር በንቲም ቢሆን  የስ-ነመለኮት ምሩቅ ነው እንጂ የታሪክ ሙሁር አይደለም፡፡ ስለዚህ በእርሱ የቀረበውን የኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ የእኔን ምላሽ ለመዳኘት በሃገራችን በተለያዩ ደረጃ ያሉትን የታሪክ ሙሁራን አስተያየት እጠይቃለሁ፡፡ እንደአውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያዊነት በደም ውስጥ ስላለ ታሪክ አጥንተን የምናረጋግጠው የሩቅ ሐገር ትዝታ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት እለት እለት የሚኖርበት ስለሆነ አውቀናል ተምረናል ከምንለው በተሻለ ታሪካችንንና ማንነታችንን መናገር የሚችሉ አባቶች አሉን።

ዶ/ር በንቲ ኦጁሉ በ2017 የታተመው የጀርመን ኢቫንጀሊካን ቤትክርስቲያን መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ የኢትዮጵያ ስም እንዲወጣ ዋናውን ስራ የሰራ ሰው ነው። ዶክተሩ በሰጠው ቃለ ምልልስ ስለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ስለክርስትና እምነት እና በክርስቶስ በበማመን ስለሚገኝ የኃጢያት ስርየት ጉዳዮች መሰረታዊ እና ማንም ‹‹ተራ›› ምእመን ሊስተው የማይችለውን ስህተት ተሳስቷል፡፡ ዶ/ር በንቲ በምልልሱ ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ክርስትናን ከመቀበሉ በፊት ከክርስትና እምነት ጋር አቻ የሆነ እምነት እንደነበረው ተናግሯል፡፡ በአካባቢው አህጉራት የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት ከመምጣቱ በፊት የኦሮሞ ሕዝብ በራሱ መንገድ እግዚአብሔርን የሚያመልክ እንጂ ጣኦት አምላኪ አይደለም ብሏል፡፡ በጥናቱ ወቅትም በኦሮሞ ነባር ሃይማኖት (ዋቄፈታ) እና በክርስትና መካከል ብዙ ተመሣይነትና ጥቂት ልዩነቶችን እንዳገኘ ተናግሯል። ለዚህም ማስረጃ ሲሰጥ በክርስትና እግዜብሄር ለሚለው የፈጣሪ መጠሪያ በኦሮምኛ “ዋቃ” ወይም “ዋቀዮ” ስለሆነ ክርስትናና የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ እምነት አብረው መጓዝ የሚችሉ መሆናቸውንም በኩራት ይናገራል።  መጽሃፍ ቅዱስን ወደ ኦሮሞኛ ሲተረጎም “God” የሚለውን የፈጣሪ ስም በኦሮምኛው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዋቃ” በሚለው መተካቱ የኦሮሞ ነባር ሃይማኖት ከክርስትና ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑ እንደማስረጃ አቅርቦታል።

ክርስትና የመጣው ከክርስቶስ ሞትንና ትንሳኤ በኋላ ስለሆነ ክርስቶስ ሳይኖር ክርስትና በዓም ሁሉ ጭራሽ አልነበረም፡፡ ወንጌልም የተጀመረው የክርስቶስን አዳኝነት በመንገር እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ወንጌልን ሳይሰማ ክርስቶስን ሳያምን እግዚአብሔርን ያመልክ ነበር ብሎ መናገር በህዝቡ መሳለቅ ነው፡፡ ክርስቲያንነት ከክርስቶስ ሞትን ትንሳኤ በኋላ የመጣ እምነት እንደሆነ እንኳንስ መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ ያነበበ ቀርቶ እመነት የለሽ (ኤቲየስት) የሆነ ሰው ያውቀዋል፡፡ በሐዋ. 11፣26 ላይ ‹‹ሐዋርያትም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተብለው ተጠሩ›› ይላ፡፡ በሐዋርያት ስራ 8፣26-40 ባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ደግሞ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የተጠመቀው በወንጌል ካመነ በኋላ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ግሪኮች፣ ሮማውያኖች፣ አሜሪካኖች፣ ጀርመኖች እንዲሁም ሌሎች የአለም ሕዝቦች በሙሉ ወንጌልን ሰምተው ጌታን ከማወቃቸው በፊት ሁሉም ጣኦት አምላኪዎች ነበሩ፡፡ ይህን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን የአርኪኦሎጂ ምርምሮችም ይመሰክራሉ፡፡ ክርስቶስን የማያውቅ ሕዝብ በጨለማ እንደሚኖር ኤፌሶን 2 በስፋት ይናገራል፡፡ በሮሜ 3፣ 10-11 ላይ ደግሞ ‹‹ጻድቅ ማንም የለም፤ እንድም እንኳ አስተዋይ የለም፡፡ ሁሉም ተሳስተዋል፣ ባንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል›› በማለት አይሁድም ሆኑ ሌሎች የአለም ህዝቦች በሙሉ ከሐጢያት በታች እንደሆኑ ይናገራል፡፡

ሰው ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ እርቅ ያደረገው በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ በኋላ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ከጫፍ እስከ ጫፍ ይተርካል፡፡ ክርስትና ከዘርና ከጎሳ በላይ የሆነ  ሁሉንም ህዝብ በክርስቶስ አንድ የሚያደርግ እውነት ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝቦችም ሆኑ ሌሎች የኢትዮጵያ ቤሔሮች የሚያኮራና በዘመናት የዳበረ ባህል እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ደግሞ እንኮራበታል፡፡ የእግዚአብሔር ጽድቅ ግን ክርስቶስን በማመን ብቻ የሚገኝ እንደሆነ እንጂ በባህልና በወግ እንደማይገኝ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እጅክ በርካታ ስፍራ እንደተጻፈ ዶ/ር በንቲ አለማወቁ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ይህ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ሳያምን እንዴት ፓስተር እንደሆነ ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን የኦሮሞ ሕዝብ ባህል የከበረ እና ተወዳጅ ቢሆንም ከክርስትና እምነት ጋር ምንም ተመሳሳይነት የለውም፡፡

ዶ/ር በንቲ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ያደረገውን ‹‹ጥናት›› ዲሴምበር 2016 ሒልደሺም ዩኒቨርሲቲ ቀርቦ ጁን 2017 እንዳለፈ ተናግሯል፡፡ ምንም እንኳን አላማው የተጣመመ ቢሆንም የዶክትሬት መመረቂያ ጽሁፍ ያውም በባእድ ቁዋንቋ ማቅረብ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ስለማውቀው እንኳን ደስ ያለህ አላለሁ። ስለኦሮሞ ህዝብና ስለኢትዮያ ታሪክ የጥናት ጽሑፍ መመርመርና መፍረድ የሚችሉ ጀርመኖች አይደሉም፡፡ ዶ/ር በንቲ የኦሮሞ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ ታሪካችንን እንደፈለገ የማቆሸሽ መብት የለውም፡፡ በስደት በሚኖርበት ምድር ገንዘብና አጋጣሚውን ስላገኘ እድሉን ለክፉ አላማ ባያውለው መልካም ነበር፡፡ ዘላንነት እጣ ፈንታችን ሆኖ በባእድ ሐገር እንኖራለን እንጂ ሐገርን መካድ ክብር አይደለም፡፡

ዶ/ር በንቲ በፓስተርነት እየሰራ ያለበት ኢቫንጀሊካል ደችላንድ ቤትክርስቲያን ባሳተመው አዲስ የአማርኛ ትርጉም መጽሃፍ ቅዱስ ላይ ቀደም ሲል በነበረው ቅጂ ውስጥ “ኢትዮጵያ ” የሚለውን ቃል “ኩሽ” በሚለው ቀይሮታል። በቀደመው ትርጉም ውስጥ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን ስያሜ ዶክተሩ ‹‹ስህተት›› እና ‹‹ጊዜ ያለፈባቸው›› ናቸው ብሎታል።

በቀድሞዎቹ የመጽሃፍ ቅዱስ  ህትመቶች  ውስጥ የሚገኙ የትርጉም ጉድለቶችንና ግድፈቶችን እያሻሻሉ ማቅረብ የተለመደ አሰራር ስለሆነ በራሱ ችግር የለበትም። በአሁኑ ወቅት ከ 60 በላይ የሚሆኑ የእንግሊዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አሉ፡፡ እነዚህ ትርጉሞች በሙሉ በቃላት አጠቃቀም፣ በሰዋሰውና በአረፍተ ነገር አገባብ ይለያያሉ እንጂ መሰረታዊ የሆነ የኃሳብ ልዩነት የላቸውም። ለምሳሌ በቀድሞው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባያዎች የሚለውን ሰራተኞች፣ ወዛደሮች፣ ባለሙያዎች እና በመሳሰሉት ቃላት ለውጠውታል፡፡ በዚህ በቀድሞው ዘመን ሰው ለሌላ ሰው ተቀጥሮ የሚሰራና የሌላውን ሰው ጥቅምና ፍላጎት በማሟላት የሚኖር ሁሉ ባሪያ ነው የሚባለው፡፡ ከዚህ በፊት በአማርኛ የተተረጎሙት ቅጂዎችም አንዳንድ ከጊዜው ጋር የማይሔዱ ቃላትን ሕብረተሰቡ በሚያውቃቸው ቃላት ለወጧቸው እንጂ መሰረታዊ ኃሳቡ ተመሳሳይ ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ከዚህ በፊት አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለግል ጥቅም፣ በሕዝብ ጥላቻ፣ ወይም የፖለቲካ አጀንዳ መሰረት ተደርጎ አልተተረጎመም።

ዶ/ር በንቲ ሲያስረዳ ብሉይ ኪዳን ከሂብሩ ቋንቋ ወደ ግሪክ ሲተረጉሙ “ኩሽ” የሚለውን ወደ “ኢትዮጲስ” በመቀየር ስህተት ሰሩ ብሏል። ‹‹ኢትዮጲስ›› ማለት “ፊቱ የተቃጠለ ህዝብ” ማለት ስለሆነ እኛ ጥቁር ሕዝቦችን ሊሰድቡን ፈልገው ኩሽ የሚለውን በ ‹‹ኢትዮጲስ›› ለወጡት ብሏል። ስለዚህ በቀደመው የመጽሃፍ ቅዱስ ቅጾች ውስጥ “ኢትዮጵያ”  የሚለው ቃል በሙሉ ወደ ኩሽ እንዲለወጥ ጥሯል። በዶክተሩ ጥናት ‹‹ኢትዮጵያ›› ማለት ክብርን የሚነካ የሚያዋርድ (Derogatory) መጠሪያ ነው ብሏል፡፡ ግሪኮችም መጽሐፍ ቅዱስን ሲተረጉሙት ጥቁሮችን ለማዋረድ ብለው ኩሽ የሚለውን ስም በኢትዮጵያ እንደቀየሩት ደርሼበታለሁ ይላል፡፡

በዶ/ር በንቲ ትንታኔ ኢትዮጵያዊ መባል የሚያኮራ ሳይሆን ሞራልን የሚነካ ስድብ እንደሆነ ያስባል፡፡ ለምሳለሌ በኤርሜያስ 13:23 ውስጥ ” ኢትጵያዊ  ቆዳውን ነብር ዥጉርጉርነቱን ይቀይራልን?” የሚለውን ቃል ላይ “ኢትዮጵያ ” የሚለው ቃል ፈጽሞ ሊጠቀሙበት የማይገባ  ስድብ (Insult) ስለሆነ ‹‹ኩሽ›› በሚው ለውጦታል። በርግጥ ክፍሉ አዎንታዊ ሳይሆን አሉታዊ መልእክት ያለው ቃል ነው፡፡ በዚህ ክፍል የተጻፈው ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ማለት ስድብ ከሆነ ‹‹ኩሽ›› ሲሆን ስድቡ ይጠፋል? ወይስ ኢትዮጵያውያኖች ለብቻችን እንዳንሰደብ ፈልጎ ለመላው አፍሪካ ለማዳረስ ነው ‹‹ኩሽ›› ያደረገው?

ከዚህ በፊት የታተሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጥቁር ሕዝብ መግለጽ ሲፈልኩ ኩሽ የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ፤ ኢትዮጵያውያንን ብቻ መግለጽ ሲፈልጉ ደግሞ ኢትዮጵያን ይጠቀማሉ፡፡ በዘፍ. 10፣ 6-20 ውስጥ ናምሮድ የኩሽ ልጅ እንደሆነ ተገልጾአል፡፡ ኩሽ ማለት ደግሞ ጥቁር ሕዝብ የሚለውን ለመተካት የገባ ቃል ነው፡፡ ሙሴ ያገባት ሴት ኢትዮጵያዊት እንደነበረች መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ፍልስጤም፣ ከነአን፣ ግብጽ፣ ሊባኖስ፣ እስራኤል፣ ሕንድ የሚሉትን ስሞች ብንመለከት የአህጉር መጠሪያ ሳይሆኑ የሐገር መጠሪያ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሙሴን ሚስት ኢትዮጵያዊ ማለቱ ወይም በሐዋርያት ስራ ላይ የተጠቀሰው ጃንደረባ ኢትዮጵያዊው የተባለው በቀለማቸው ጥቁሮች ስለሆኑ ሳይሆን በትውልዳቸው ኢትዮጵያውዎች ስለሆኑ ነው፡፡

ዶ/ር በንቲ ስህተት ነው በሚለው መዝሙር 68፣31 ላይ ያለውን ሙሉን ቃል ብንመለከተው ‹‹መኳንንት ከግብጽ ይወጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› ይላል፡፡ እንግዲህ ግብጽ የምትገኘው አፍሪካ ውስጥ (ጥቁር ምድር) መሆኑ እየታወቀ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል በኩሽ መለወጥ ቃላትን መደረት አይሆንም? በዶ/ር በንቲ ትርጉም ከተለወጠ ‹‹መኳንንት ከኩሽ ይወጣሉ፤ ኩሽ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› መባል ነበረበት፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፡፡ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ስለመላው ጥቁር ሕዝብ ነው የሚናገረው የሚሉ ትርጉሞችን ሰምቻለሁ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢትዮጵያ ተብሎ የተጠቀሰው መላውን አፍሪካ፣ በተለይ ደግሞ መካከለኛውንና ምስራቅ አፍሪካን ያጠቃልላል ሲባል ሰምቻለው፡፡ እንደዚሁም፣ በጥንት ጊዜ ኢትዮጵያ እስክ ግብጽ ድረስ ያሉትን ሐገሮች ታገዛ ስለነበር ነው የሚባልም ግንዛቤ አለ፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ኢትዮጵያ ማለት የጥላቻ ወይም የስድብ ስም መሆኑን ለመጀመሪያ በእፍረት ሲናገር የሰማሁት ዶ/ር በንቲ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነትም ሆነ ጥቁርነት ክብር እንጂ ዶ/ር በንቲ እንደሚለው ውርደት አይደለም፡፡ ለአብርሐም ተስፋ የተገባለት የከነአን ምድር የጥቁሮች ምድር እንደሆነ ታሪክም የከርሰ ምድር ምርምርም ያረጋግጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትንቢተ ሰፎንያስን የጻፈልን ነብይ ጥቁር (የኩሽ ዘር) ቢሆንም በእየሩሳሌም የሚኖር እስራኤላዊ መሆኑ በምእራፍ 1 ተገልጾአል፡፡ በመኃልየ መኃልየ ዘሰለሞን 1፣5 ላይ የተጠቀሰችው ሱናማጢስ ሴት፣ በ2ኛ ሳሙኤል 11፣ 3 ላይ ያለችው የሰለሞን እናት ቤርሳቤህ፣ በ 1ኛ ነገ. 10፣ 1 ላይ የተጠቀሰችው የሳባ ንግስት፣ በማቴዎስ 27፣ 32 ላይ የተጠቀሰው ቀሬናዊው ስምኦን ፣ በሐዋ. 8፣37 ላይ የተጠቀሰው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ እና ሌሎችም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በቆዳ ቀለማቸው ጥቁር ቢሆኑም ኢትዮጵያና ኩሽ የሚለውን ቃል ግን በተለዋዋጭነት አልቀረበም፡፡

ዶ/ር በንቲ ሌላ ፍላጎት ከሌለው በቀር ኢትዮጵያ ማለት በአለም ላይ ስድብ ሆኖ የታወቀበት ታሪክ የት ነው ያገኘው? እንዴት አይነት ጥናት ቢያደርግ ነው ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በመደምሰስ ሊያስከብረን የፈለገው? ምእራባውያኖች ‹‹በእብደት እና በሊቅነት መካከል ያለው ልዩነት የቀጭን ክር ያህል የሰለለ ነው›› (There is a thin line between genious and insanity) እንደሚባለው ብዙ መመራመር ወደእብደት እንዳይለወጥ እፈራለሁ። በ2016 ዓ.ም በተደረገው ቆጠራ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ 636 የዓም ቁዋንቋዎች ተተርጎሟል፡፡ አዲስ ኪዳን ብቻ ደግሞ በ 1442 ቁዋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡ ከዚህ ሁሉ ትርጉም  ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን ስም በመሰረዝ የዶ/ር በንቲ መጽሐፍ ቀዳሚውና ብቸኛው መጽሐፍ ይሆናል፡፡

በዶ/ር በንቲ ‹‹ጥናት›› ውስጥ በሂብሩ፤ በግሪክ፤ በእንግሊዝኛ በጀርመንና በሌሎችም ቋንቋዎች የበቁና ከፍተኛ እውቀት ያካበቱ  የስነመለኮት ሰዎች እና የስነቋንቋ ጠበብት እንደተካተቱ ተናግሯል። አዲሱን የትርጉም ስራ ለጀርመኑ ጳጳስና በጀርመን የሚገኙ የኢቫንጀሊካን ቤተክርስቲያን ተወካዮች እንደተሰጠ በቃለ ምልልሱ አብራርቷል። ስለኦሮሞ ሕዝብ ለማጥናት የሐገሬው ተወላጆች መሐል ገብቶ የሕዝቡን ባሕልና ታሪክ ማወቅ ከብዙ ስህተት በጠበቀው ነበር፡፡ በጀርመን ያሉ የፕሮቴስታንት ቤተክርስትያናት በአዲሱ ትርጉም ደስተኞች መሆናቸውን በቃለ ምልልሱ ገልጾአል። በጀርመን ያሉት የሌላ ሐገር ዜጎች ምን እንደሚሉ ባለውቅም በጀርመን ያሉ ኢትዮጵያዊ ፕሮቴስታንት እምነት ተከታዩች ግን በጉዳዩ ማዘናቸውን በተለያየ መንገድ ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡

ዶ/ር በንቲ ይህ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ የካቶሊክ ወይም የኦርቶዶክስ ሳይሆን የፕሮተስታንት ቤተክርስቲያን መጽሃፍ ቅዱስ ነው ብሏል። ፕሮተስታንቶች የምንጠቀምበት 66 መጽሃፍት ካቶሊኮችና ኦርቶዶክሶች ከሚጠቀሙበት 66 መጽሐፍት ጋር ፍጹም ተመሳሳይ ነው፡፡ ካቶሊኮች ሌሎችን መጻሕፍት ጨምረው  73 ሲኖራቸው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ደግሞ 81 መጽሐፍትን ትጠቀማለች። ይህ ማለት ግን ዶ/ር በንቲ እንደሚናገረው የፕሮቴስታንት እምነት የራሳቸው የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ስለፈጠሩ አይደለም፡፡ የፕሮቴስታንት ጀማሪና አባት የሚባለው ማርቲን ሉተርም ቢሆን ቃሉ የሚለውን በትክክል ተረጎመው (አነበበው) እንጂ አዲስ መጽሐፍ ይዞ አልተነሳም፡፡ ይህ የዶ/ር በንቲ መጽሐፍም እርሱ እንዳሰበው በመላው ዓለም ያሉትን የፕሮተስታንት ቤተክርስቲያን አይወክልም። እርሱ ተጠግቶ በሚሰራበት የጀርመኖች ቤተክርስቲያን ገንዘቡና አቅሙ ስላላቸው ይህንን አዲስ መጽሐፍ እያሳተሙ በነጻ እንደሚድሉ ይታወቃል፡፡ በቢሊዮኖች በሚቆጠር ቅጂ ቢታተም እንኳን የመጽሐፉን ስህተት አይሻሽለውም፡፡ ውሽት የቱንም ያህል ተደጋግሞ ቢነገር እውነት አይሆንም፡፡

ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ፣ በአሜሪካን ሐገር የሚገኝ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አሳታሚ ድርጅት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የሚቃወሙ ክፍሎችን ለቀሞ በማውጣት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ድርጅት የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ እነዚህ ስሞች የሰውን ስብእና የሚነኩ ናቸው ይላሉ፡፡ እንዲሁም፣ የመጀመሪያዎቹ ተርጓሚዎች ተሳስተው እንጂ ቃሉ እንደዚህ እንደማይል በጥናት ደርሰንበታል የሚል ነው፡፡

ዶ/ር በንቲ የራሱን እና አጠገቡ ሆነው ትምህርቱን እንዲጨርስ በገንዘብ የረዱትን ድርጅቶች አቋም ሊወስድ ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የእርሱን ‹‹ጥናት›› የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን እምነት እንደሆነ መናገሩ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ አኛ እንደሌሎቹ ኢትዮጵያን ከአባቶቻችን ጉያ የተፈጠርን ወንድና ሴት ኢትየጵያውያኖች ነን እንጂ ምድሪቱን ለማሳደፍ የተነሳን ጉዳንጉዶች አይደለንም፡፡

የዶ/ር በንቲ ጥረት ስውር አላማ እንዳለው ወደማመን ያደረሰኝን ዋና ነጥብ ላንሳ፡፡ በዶ/ር በንቲ እምነት ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ከምባታ፣ አገው፣ ሃዲያ፣ ሶማሌ እና ሌሎችም ወገኖች የኩሽ ዘሮች ናቸው እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደሉም ብሎናል፡፡ የኦርቶዶክስና ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናትም ወደዚህ ሕዝብ መሐል ሄዶ መስራት ከፈለጉ ህዝቡን በሚመለከተው ስም ኩሽ እያሉ እንጂ ኢትዮጵያዊ እያሉ መጥራት እንደሌለባቸው ይመክራል፡፡ ኢትዮጵያዊ ማለት “ፊታቸው የተቃጠለ ሰዎች “ ማለት ስለሆነ ይህ መጠሪያ ክብረ ነክና አዋራጅ ስድብ ነው ይላል ዶክተሩ። ቃላት በዘመናት መሐል ተሸክመውት የሚዘልቁት ለዓለም ሕዝብ የሚሰጡት ትርጉም አላቸው፡፡ አንባቢዎቼ ኢትዮጵያዊያኖች ስለሆናችሁ እራሳችሁ ፍረዱ፡፡ ኢትዮጵያዊ መባል በአለም የሚያዋርድ ስም ነው? ለሐገራቸው ከተሰውት እነ አብዲሳ አጋ ጀምሮ በዓለም ላይ ስሟን ያስጠሩት ሯጮቻችን፣ እንዲሁም በመላው ዓለም በተለያየ የምርምር ስራ ላይ አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉት ወገኖቻችን በኢትዮጵያዊነታቸው አላኮሩንም? እንደ ዶ/ር በንቲ በዚህ ስም አፍራችሁ ታውቃላችሁ?

በዶ/ር በንቲ ‹‹ጥናት›› መሰረት ኢትዮጵያ ከሚለው ቃል ጋር የሚዛመድ ህዝብም ፤ ቦታም ፤ ቋንቋም ስለሌለ ዩኒቨርሲቲዎች  ውስጥ የሚደረጉ የኢትዮጵያ ጥናት መቆም እንዳለበት ይናገራል። መቼም ሐገርን በተለያየ ምክንያት መክዳት በእርሱ ስላልተጀመረ አይስገርምም፡፡ ጣልያኖች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ ሕዝቡን ለብዙ ችግር የዳረጉት የሐገሬው ተወላጅ ባንዳዎች እንደነበሩ ከታሪክ እናያለን፡፡ ዶ/ር በንቲም ቢያንስ ኢትዮጵያ የምትባል ሐገር እንዳለች ሕዝቦቹም በስማቸው እንደማያፍሩ ከጣሊያኖች መጠየቅ ይችላል፡፡

ኢትዮጵያ ማለት በሰሜን አፍሪካ የምትገኝ ሐገር ማለት እንጂ የስድብ ስም እንዳልሆነ ከዶ/ር በንቲና ለትምህርቱ በገንዘብ ከረዱት የጀርመን ድርጅቶች በቀር መላው ዓለም ያውቃል፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስም በቅርብ ጊዜ የተፈጠረ ሳይሆን ከሁሉም የአፍሪካ ሐገር ስሞች ቀድሞ የነበረ እንደሆነ ለማረጋገጥ ካስፈለገ በ1780 ዓ.ም የታተመውን የአፍሪካ ካርታ መመልከት በቂ ይሆናል፡፡ ዶ/ር በንቲ እንደሚለው ኢትዮጵያ የሚለው ስም በቅርብ የተፈጠረ ሳይሆን እንደውም የአብዛኛውን የአፍካ ክፍል መጠሪያ ነበር፡፡ በየዘመናቱ ሌሎቹ የአፍሪካ ክፍሎች የራሳቸውን ክልልና የራሳቸውን አዲስ ስም ሲያወጡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ግን ስሙን ይዛ ቀርታለች፡፡ ይሄንን ለማረጋገጥ የሚፈልግ ማንም ሰው በመረጃ መረብ (ኢነተርኔት) ላይ ‹‹የአፍሪካ የድሮ ካርታ›› (Africa old map) ብሎ ቢፈልግ በርካታ ጽሁፎችን እና ካርታዎችን ያገኛል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚያሳፍር ስድብ አለመሆኑን ለሐገራቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉትን ቁርጠኛ ኦሮሞ ፤ ሶማሌ፤ አፋር፤ እና ሌሎችም ልጆች ሔዶ ቢጠይቅ በተሸለ ያስረዱታል፡፡

ዶ/ር በንቲ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያውቀው ከዳግማዊ ሚኒሊክ በኋላ ያለውን እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ ያቀረበው ከ1900 በፊት የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ስነ መልክአምድር (ካርታ) አልነበረም ብሎ ነው። ከዚያ በፊት ህዝቡ ኦሮሞ፤አማራ፤ሲዳማ ፤ አፋር፤ ትግሬ ወዘተ….ይባሉ ነበር እንጂ ኢትዮጵያውያኖች አልነበሩም ይለናል። ኢትዮጵያ የሚለው ስም በሕገ መንግስት ውስጥ የገባው በ1931 ዓም በንጉስ ኃይለስላሴ ዘመን ነው ይለናል፡፡ በዶ/ር በንቲ ስሌት ኢትዮጵያ የ 86 ዓመት እድሜ ያላት ሐገር ናት እንጂ ከዛ በፊት አትታወቅም፡፡ ይህ ስህተት መሆኑን ለማረጋገጥ ለዶክትሬት የሚያበቃ ጥናት ከሚያደርግ የገዛ ወላጆቹን ቢጠይቅ ይነግሩት ነበር፡፡ ዳግማዊ ምኒሊክና ኃይለ ስላሴ የኢትዮጵያን ካርታ እንደገና ከለሱት እንጂ ካርታውን ሲሰሩ የመጀመሪያዎቹ አልነበሩም፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዲግ መንግስት የኢትዮጵያን ካርታ ድጋሚ ከልሶት ቀድሞ በክፍለ ሐገር የተከፋፈለውን አሁን በክልል ለይቶታል፡፡ አሜሪካ እና ሌሎችም የሰለጠኑት ሐገሮች መልክዓ ምድራዊ ካርታቸውን በተለያየ ጊዜ ከልሰውት እንጂ ዛሬ ላይ ያላቸውን ካርታ በአንድ ለሊት አላመጡትም፡፡

ኢህአዲግ የኢትዮጵያን መንግስት መምራት ከጀመረ በኋላ ኢትዮጵያ የ300 አመት ታሪክ ብቻ ነው ያላት የሚሉ ሰዎች መነሳታቸውን አውቃለሁ፡፡ ከዚህ መንግስት ስልጣን መያዝ ተከትሎ ምድሪቱን በዘርና በጎሳ የመከፋፈል ወረርሽኝ እርስ በእርስ እንዳስተላለቀን ይታወቃል፡፡ አሁን በምድራችን ያለው መንግስት ብዙ ጥሩ ስራዎችን የሰራ ቢሆንም ሕዝቡን በዘርና በጎሳ መከፋፈሉና እርስ በእርሱ እንዲጠላላ ማድረጉ በዘመናት የማይረሳ ትልቅ ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ሕዝብ እርስ በእርሱ ተከፋፍሎ አንዱ በሌላው ላይ ሲነሳ መንግስት የራሱን ዘመን ለማራዘም የሚጠቀምበት ያረጀ ያፈጀ የ18ኛው ክፍለ ዘመን ‹‹የከፋፍለህ ግዛ›› ስልት ነው፡፡ ዶ/ር በንቲ ግን 300 ዐመት ታሪኳንም ክዶ ኢትዮጵያዊነትን ወደ 86 ዓመት በማምጣት ምን እንደሚጠቀም ወይም ምን አይነት ጥላቻ ነፍሱን አንቆ ቢይዛት እንደሆነ አልገባኝም፡፡

ኩሽ የመላው አፍሪካ (ጥቁር ሕዝብ) መጠሪያ መሆኑ እየታወቀ ሁሉም የአፍሪካ ሐገሮች የራሳቸው ልዩ መጠሪያ እንዳላቸው ማንም የአምስተኛን ክፍል የህብረተሰብ ሳይንስ የተማረ ሰው ያውቀዋል፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ ብቻ በዛው በኩሽ መጠራት ያለባት ለምንድነው? ዶ/ር በንቲ እኛ ኦሮሞዎች ኢትዮጵያዊ አይደለንም የሚለውን ዘመን አመጣሽ ክህደት ለማጠናከር ብሎ እየተከራከረ ከሆነ ሓሳቡን በዚሁ መንገድ ማስተናገድ ይቻላል፡፡ ይህ አመለካከቱ አርሱን ወይም ጥቂት ግለሰቦችን የሚወክል እንጂ እንደኦሮሞ ተወላጅነቴ ቢያንስ አኔን እና በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩትን የኦሮሞ ተወላጆች አይወክልም፡፡ ሁላችን ኢትዮጵያዊ ሆነን ተወልደናል፣ ኢትዮጵያዊ ሆነን እንሞታለን። ወንጌል ደግሞ ከዚህ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡

ዶ/ር በንቲ ኩሽ ነኝ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ብሏል፡፡ ከሆድ የወጣ ሁሉ ልጅ ስለማይሆን እርሱ አይደለሁም እያለ በግድ ኢትዮጵያዊ ነህ ማለት አግባብ አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር በንቲ እንደዚህ አይነት ክፉ ዘር በምድሪቱ ላይ እየዘራ ተቻችለን እንድንኖርም ምክሩን ለመለገስ ሞክሯል፡፡ ተቻችሎ የኖረውን ህዝብማ እርሱና ቢጤዎቹ ደም አያቃቡት እንደሆነ ቢያስተውል መልካም በሆነለት ነበር፡፡

ዶ/ር በንቲም ዘመንህን ሁሉ ለተሳሳተ አላማ በማዋልህ በጣም አዝናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ብተክርስቲያን ሰው ለመዳን ጌታን እንደግል አዳኙ መቀበል እንዳለበት አበክራ ከመናገር በቀር ከኦርቶዶክስና ካቶሊክ እምነት የተለየ ሌላ ወንጌላ የላትም፣ ሌላ ክርስቶስንም አታስተምርም፡፡ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትም ይህንን የዶ/ር በንቲ መጽሐፍ እንዳይጠቀሙ በኢትዮጵያ ውስጥም ያሉ የመጻሕፍት መደብሮች እንዳያሰራጩት የበኩሌን ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

To download this article, please click here: Response to Removal of the name Ethiopia from the Bible

To Read Dr. Benti’s interview: http://www.ethiomedia.com/1000bits/getting-the-name-ethiopia-erased-from-bible.pdf