ሰው አምላክ ይሰራል ዛሬም እንደጥንቱ
ጠርቦ ያስቀምጣል በልቡ በቤቱ፤
ይሸላልመዋል በጨርቅ በክራባት
ይወለውለዋል ጥብቅና ቆሞለት።
እሾህ ከሞላበት መረን ከበቀለ
ከተጣመመ ልብ አመጻን ካዘለ
ሰዎችን ይጠርባል ቀርጾ ሊያመልካቸው
ነብይ ሐዋርያ ምንትስ ሊላቸው።
እርሱ በሌለበት አምልኮ አይደምቅም
ሐዘን ይላበሳል አንድም ሰው አይስቅም።
አቤት መመሳሰል!
ገላውን ባይፍቅም ባይቆስል ደረቱ
እውቀቱን ገንዘቡን ይገብራል ስንቱ!
እውነት ከሆነማ ወንጌሉ የሚለው
እነዚህ አምላኮች በድን ብቻ ናቸው።
ጆሮ አላቸው እንጂ አይሰሙም አይለሙም
ለዚህ ሁሉ ጩኸት ምላሽ የላቸውም።
እንደቀድሞው ዘመን ቂቤ ባንቀባቸው
አይንቀሳቀሱም እውነት በድን ናቸው።
[ኦክቶበር 14፣ 2017 ከሚመረቀው የወንዝ ዳር ህልሞች መጽሐፍ ውስጥ የተወሰደ]
Recent Comments