ዛሬም ወንጌልን ትምክህታቸው ያደረጉ፣ ቅድስናን አላማቸው ያደረጉ፣ ግባቸው እውነተኛውን የመዳን ወንጌል ለአለም አብስረው ማለፍ የሆነ ለጣኦታት ያልሰገዱ ቅሬታዎች በተለያየ ክፍል በትጋት እያገለገሉ ናቸው፡፡ ስለነዚህ እውነተኛ ምስክሮች ጌታን እናመሰግናለን፡፡ በሌላ በኩል፣ ወንጌልን መነገጃ ያደረጉ፣ ሁዳቸው አምላካቸው የሆነባቸው፣ ተስፋቸውን በምድር ብቻ አድርገው በጨለማ እየሳቱ ህዝቡን የሚያስቱ የዘመኑ ዴማሶች ከመችውም ዘመን ይልቅ በዝተው ማየት የተለመደ ሆኖአል፡፡ በዙረያችን ካሉት ‹‹አገልጋዮች›› ቁጥራቸው በርካታ የሆነ በዝሙት፣ በገንዘብ ወይም በሞራል ውድቀትና በዘቀጠ ሕይወት ይታማሉ፡፡ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑትም ከሚያገለግሉት ምእመን ባነሰ መንፈሳዊ ሕይወት ይመላለሳሉ፡፡

አላማችን ቤተክርሰቲያንን ለማጥራትና በትምህርትና በስራ የበረታ ትውልድ ማፍራት ነው

በዚህ የጽናት አገልግሎት ቤተክርስቲያንና የቤተከርስቲያን መሪዎች ተጠያቂነትንና ሐላፊነት ያለውን አገልግሎት እንዲያገለግሉና ምእመኑ ስለአገልጋዮቹ ምንነት፣ እምነት፣ ስራና የጽድቅ ኑሮ እየገመገመ የተገኙ መረጃዎችን በሙል ለምእመኑ ለማድረስ የታሰበ ነው፡፡ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ያሉ ኢትዮጵያን አገልጋዮች ከተሰጣቸው የጸጋ አገልግሎት ባሻገር በኑሮና በሞራል ምሳሌነት ያለው ሕይወት በመኖር ለስራቸው ተጠያቂነት ባለው መንገድ ራሳቸውንና ሌሎችን እንዲያተርፉ በትጋት ይሰራል፡፡ በዚህ ረገድ የጽናት አገልገሎት ከማንኛውም የቤተክርስቲያንና መንፈሳዊም፣ መንፈሳዊ ያልሆነም ድርጅት ነጻና ገለልተኛ በመሆን ለሁሉም ድርጅቶች ሚዛናዊ የሆነ ግምገማ ይሰጣል፡፡

የወንጌል አማኞች በሐገር ውስጥና በተለያዩ የአለም ክፍሎች ባሉ የብያተክርስቲያናት ሕብረት ታቅፈው ወጥ የሆነና መቀባበል ያለበት አገልግሎት እንዲኖር ከፍተኛ ግፊት ያደርጋል፡፡ የአብያተ ክርስቲያናት ሕብረት አባላትን ዝርዝር ለምእመኑ ያቀርባል፡፡  በዚህም መሰረት በሞራልና በዲሲፒሊን ምክንያት ከአገልግሎት የታገዱ፣ የተባረሩና ክፉ የህይወት ምስክርነት ያላቸው አገልጋዮች ከአንዱ ቤተክርስቲያን ወደሌላው እንደልባቸው በመዘዋወር ምእመኑን እንዳይበርዙ ይከላከላል፣ ይጠቁማል፣ ያወግዛል፣ ያጋልጣል፡፡ በመላው አለም የሚገኙ ክርስቲያኖችን በዚህ ድህረ-ገጽ በመጠቀም ስለሚገለገሉበት ቤተክርስቲያንና ስለሚያገለግሉአቸው ሰዎች መንፈሳዊ አካሔድ ሚዛናዊ የሆነ መረጃ ይሰጣል፡፡ በተጨማም፣ በተለያዩ ሐገሮች የሚገኙትን የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ሕብረትም ከአድሎና ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ ስለመስራቱ ይገመግማል፣ ለሁሉም አባላትና ምእመን ገለልተኛ የሆነ መረጃና አመታዊ ሪፖርት ይሰጣል፡፡

ከአብያተክርስቲያናት፣ ከአገልጋዮችና ከሌሎች ወገኖች ጋር በመተባበር አመታዊ ኮንፍረንሶችንና ወርክ ሾፖችን በማዘጋጀት ወንጌል ሳይበረዝና የሐዋርያትን መሰረት ሳይለቅ ለምድራችን ሊደርስ የሚችልበትን መንገድ ይተልማል፡፡ አጫጭር ትምህርቶችን በድህረ ገጻችን እናሰራጫለን፡፡ ለቀጣዩም የሐገሪቱን የወንጌል አሰራር በተመለከተ ራእይ እንነድፋለን፣ እንወያያለን፡፡ በተጨማሪም በነዚህ አመታዊ ስብሰባዎች ላይ ባለፈው ዘመናትና በአሁኑም ዘመን ለወንጌል ዋጋ የከፈሉና እየከፈሉ ያሉትን አገልጋዮች ያበረታታል፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶ የአቅምና የሐይል ጉልበት ስናገኝ ለነዚህ ወገኖች ሽልማቶችንና ማበረታቻዎችን ይሰጣል፡፡ በዚህ ጋጣሚ፣ ለዚህ አላማ ግብ መድረስ በጽሁፍና መረጃ በማሰባሰብ ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ ወገኖችን በሚከተለው ኢሜል እንዲያገኙን ጥሪ አቀርባለው፡፡ Tsinat.org@gmail.com

በኤፌሶን 415 ላይ ጳዉሎስ እውነትን በፍቅር እየተነጋገርን እራስ ወደሆነው ወደክርስቶስ በነገር ሁሉ እንደምናድግ ይናገራል፡፡ የጽናት አገልግሎት ዋንኛ አላማው ቤተክርስቲያንን መገንባት እንጂ ማፍረስ አይደለም፡፡ አገልጋዮች በጸጋቸው እንዲያገለግሉ ለማበረታታት እንጂ ጸጋቸውን ለመድፈን አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተደጋጋሚ በሞራልና ስነምግባር ውድቀት ውስጥ ሆኖ ህዝቡን ወደመንፈሳዊ ድንዘዜ የሚመራን ‹‹አገልጋይ መገሰጽና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌላቸውን ክፉ ልምምዶች ማጋለጥ የማነጽ አንዱ ክፍል እንደሆነ  እናምናለን፡፡

ይህ አገልግሎት መሰረታዊ የእምነት አቁዋም መመዘኛ ፎርም በማዘጋጀት ለአገልጋዮችና ለቤተክርስቲያን መሪዎች በቀጥታ እንዲደርስ በማድረግና ከነርሱ ያገኘነውን መረጃ በማሰባሰብ ለምእመኑ እናደርሳለን፡፡ ምእመኖች ስለቤተክርስቲያኖችና ስለ አገልጋዮቹ አንብበው የራሳቸውን ውሳኔ እንዲወስዱ እድሉን እንተዋለን፡፡ በዚህ መሰረትም አንድ አገልጋይ ወይም የአገልግሎት ድርጅት እውነትን በመናገር ለተጠሩበት ወንጌል ምን ያህል እንደሚሰሩ ለመለየትና ለምእመኑ ለማሳወቅ ጽኑ ፍላጎቴ ነው፡፡