ብዙ ጊዜ ስለቤተክርስቲያን የባለቤትነት ጥያቄ ሲነሳ ለአብዛኛው ሰው ቶሎ የሚታወሰው “ቤተክርስቲያንማ የጌታ ናት” የሚል ጠቅላላ መልስ ነው፡፡ በእርግጥ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ እንጂ የማንም አለመሆኗን ሁላችንም ብናውቅም ስለቤተክርስቲያን ባለቤትነት ወይም የይገባኛል ጥያቄዎች ሰዎች ሲሰነዘሩ መስማታችን የተለመደ ሆኗል፡፡ በክርስቶስ አምነው የዳኑትን ክርስቲያኖች ብለን ስንጠራቸው እነዚህ ወገኖች በአንድ ላይ ለአንድ አላማ የሚሰበሰቡበትን ስፍራ ቤተክርስቲያን (ኤክልሺያ) ይባላል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ቤተክርስቲያን ማለት አማኞች በአንድ ላይ ተሰብስበው የሚያመልኩበትን ስፍራ፣ የቤተክርስቲያኗን ሀብትና ንብረት፣ እንዲሁም በዛች ቤተክርስቲያን ውስጥ በአባልነት እየተገለገሉና እያገለገሉ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ያጠቃልላል፡፡

ቤተክርስቲያን በምድር ላይ የጌታን ስራ የምትሰራ ድርጅት ስለሆነች መሪዎችና አስተዳዳሪዎች ሊኖሯት ግድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በአብዛኛው ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በሽማግሌዎችና በመጋቢዎች (ፓስተሮች) እንደሚመሩ ይታወቃል፡፡ በዘመናችን በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚነሱ የተለያዩ ግጭቶችና አለመግባባቶች አንዱ ምክንያት ፓስተሮች “ይህች ቤተክርስቲያን የእኔ ናት፣ እኔ መስርቻታለሁ፣ ለእኔ ትገባኛለች” የሚሉትና የመሳሰሉት  ከጥቅም ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች መበራከታቸው ነው፡፡

በዚህ ጽሁፍ ስለቤተክርስቲያን ምንነትና ባለቤትነት ትክክለኛ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ስለ ፓስተሮች፣ ወይም “መስራቾች” በቤተክርስቲያን ንብረት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገኙት አማኞች ላይ ሊኖራቸው ስለሚገባው ባለቤትነት አብራራለሁ፡፡ የጽሁፉ አላማ መሪዎችን ለመተቸት ሳይሆን ምእመኖችን ለማስተማርና ትክክለኛ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሆነ ባክብሮት እገልጻለሁ፡፡ አንባቢዎቼም ይህንን መልእክት ሰምተው ጭብጥ ያለው ነገር ካገኙበት እንዲተገብሩት፣ ስህተትና አሻሚ ነገር ካለው ደግሞ በአድራሻዬ አግኝተውኝ እንድንማማር እጋብዛለሁ፡፡

የፓስተር ጥሪና ኃላፊነት

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ፓስተር የሚለው ስም በእብራይስጥ ራሃ (raʿah) ከሚለው ቃል የተወሰደ ሲሆን ትርጉሙም እረኛ፣ ጠባቂ ከሚለው አንድ እረኛ ለበጎቹ ሊያደርግላቸው የሚገባበውን ጥበቃና እንክብካቤ አመላካች ቃል ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይህ ጠባቂ (shepherd) የሚለው ቃል 29 ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን አብዛኛው ክፍል የሚያመለክተው የጌታን አገልገሎትና መልካም እረኛነት ነው፡፡ ለምሳሌ በሉቃስ 2 ላይ የጌታን መወለድ ያበሰሩት እረኞች እና በዮሐንስ 10፣11 ላይ ጌታ ራሱን “መልካም እረኛ” ብሎ የጠቀሰው ቃል ተመሳሳይ ትርጉም አላቸው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የፓስተርነት አገልግሎት ከሽማግሌዎች አገልግሎት ጋርም ተወራራሽ ሆኖ ስለቀረበ አብዛኛዎቹ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በመሪነት የሚያገለግሏቸውን እረኞችና ሽማግሌዎች ፓስተር ከሚለው ቃል ጋር በተለዋዋጭነት ይጠቀሙበታል፡፡

ፓስተር የሚለው ቃል መሰረቱ በላቲን ፓስኬሬ (pascere) የሚል ቃል ሲሆን ትጉሙም የሚመግብ፣ የሚሰበስብ፣ የሚንከባከብ ማለት ነው፡፡ በምእራባውያኑ አብያተክርስቲያናት “ቢሾፕ” የሚለውን መጠሪያ “ፓስተር” ለሚለው እንደ አቻና ምትክ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ በፕሮቴስታንትና የተሃድሶ አማኞች ዘንድ ፓስተር የሚለው ስም በስፋት ተግባር ላይ የዋለው በጆን ካልቭን ዘመን ሲሆን በጊዜው በካቶሊክ እምነት ካህን (priest) የሚለውን የአገልግሎት ደረጃ እንዲተካ የታሰበ ቃል ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ፓስተር የሚለው ቃል በሰለጠነው ሀገር ለአገልግሎት የሚሰማሩትን ሚሺነሪዎችም ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ባጠቃላይ ፓስተር ማለት ከጌታ በአደራ የተቀበለውን የእግዚአብሔር ህዝብ በነጻ በተቀበለው ጸጋ በታማኝነትና ምሳሌነት ባለው ህይወት አገልግሎና ጠብቆ ለመንጋው ባለቤት በታማኝነት ማስረከብ የሚችል ባለአደራ አገልጋይ ነው፡፡

ፓስተር ወይም መጋቢ አንድን ቤተክርስቲያን የመምራትና የማገልገል ጥሪ ኖሮት ከሚመራው ህዝብ በተሻለ መንፈሳዊ ብቃት ህዝቡን ወደክርስቶስ ሙላት የማስጠጋት ብቃት ያለው መሆን አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ አንድ ፓስተር የሚያገለግላቸው አማኞች በፈቃደኝነት በላያቸው ላይ መሪና ሃላፊ ሊያደርጉት ወደው የመረጡት (የሾሙት) ሰው እንጂ ስዩመ-እግዚአብሔር የሆነ ንጉስ ሊሆን አይገባም፡፡

አንዳንድ ሰዎች ፓስተር የሚለውን ቃል ከስማቸው በፊት በማስቀደም እንደ ማዕረግና ስልጣን ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ እንዳንድ ቦታ ደግሞ ፓስተር ማለት ከምእመኑ የተለየ፣ ባለስላጣን፣ ፈላጭ ቆራጭ፣ ሁሉን ቻይና፣ ሁሉን አዋቂ፣ ምእመኑ በሚወጣበትና በሚገባበት በር የማይወጣና የማይገባ ተደርጎ የሚታይበት አጋጣሚ ከጊዜ ወደጊዜ እየበዛ መጥቷል፡፡ አንድ ፓስተር ወይም አገልጋይ የተሰማራበት አገልግሎት የባርነት መሆኑን አምኖ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከምእመኑ መቀላቀል ካልቻለ አስተዋይ ምእመን እንዲህ አይነቱን ሰው በራሱ ላይ መሪው አድርጎ መሾም የለበትም፡፡ አዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ፓስተሮች በርግጥ በሪያዎች ቢሆኑም ባርነታቸው ለጌታ እንጂ ለሚያገለግሉት ህዝብ አይደለም፡፡ አገልጋዮች ባሪያዎች ናቸው ሲባል ምእመኑ እንደፈለገ የሚያዛቸው፣ እንደፈለገ የሚያወጣና የሚያገባቸው ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የአገልጋዮች ባርነት ለሾማቸው ጌታ ሲሆን ለምእመኑ ግን አብረው ለአንድ መንግስት የሚሰሩ ክቡር ስጦታዎችና ወንደሞችም እህቶችም ናቸው፡፡ አገልጋዮች የሚሸከሙት ቀንበር ከጌታ የተቀበሉን እንጂ ሰው የጫነባቸውን አይደለም፡፡ ስለዚህ ማንም ግለሰብ በገንዘቡ ወይም በስልጣኑ ወይም በዘሩና በሌላ ምድራዊ ትምክህት ምክንያት ፓስተሮችን የምድራዊ አጀንዳ እንዲፈጽሙ ማድረግ ቤተክርስቲያንን የሚያሳድፍ ነውር ነው፡፡

የቤተክርስቲያን ምእመን ባለቤት ማነው?

ፓስተሮችና መንፈሳዊ መሪዎች ሃላፊነታቸውና ተጠሪነታው በአደራ ለሚመሩት ወይም ለሚያገለግሉት ህዝብ ከሆነ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባው የስልጣንና የአገልግሎት ተዋረድ ምን እንደሚመስል መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ አማኞችን በበጎች ቢመስለንም ፓስተሮችና መሪዎች ማወቅ ያለበቻው ጥብቅ ነገር የሚያገለግሉት ምእመን አውነተኛ በግ አለመሆኑን ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ፓስተሮች ህዝቡን “የእኔ፣ የስራዬ ውጤት፣ የለፋሁበት” በማለት በዘፍጥረት 30 ላይ ያዕቆብ እንዳዋለዳቸው ሽመልመሌና ነቁጣ ያለባቸው በጎች ምእመኑን የግል ንብረታቸው የማድረግ መብት የላቸውም፡፡ የቤተክርስቲያን ምእመኖች የሚያስቡ፣ የሚናገሩ፣ የሚታዘቡ፣ የሚወስኑ፣ ከሁሉም በላይ ከፓስተሩ ጋር አብረው የሚያገለግሉ ባልደረቦቹ እንጂ ፓስተሩ በራሱ ጥበብ ተጠቅሞ ያዋለዳቸው ሲፈልግ የሚሸጣቸው፣ ሲፈልግ የሚያርዳቸው፣ ሲፈልግ የሚሾምና የሚሽራቸው የያእቆብ በጎች አይደሉም፡፡ ደግሜ እላለሁ እኛ የመንፈሱ ማደሪያ የሆንንና የዘላለም ተስፋ ያለን ሰዎች ነን እንጂ በአንድ ሰው መጎምጀት ባንድ ለሊት የተራባን ሽመልመሌና ነቁጣ ያለብን በጎች አይደለንም፡፡ በሌላ በኩል እኛ ከግብጽ የወጣን በክርስቶስ አርነታችንን ያረጋገጥን አማኞች ነን እንጂ  አንድ ሰው ሲያሻው የሚያርስብን ሲፈልግ ጡብ የሚያስጠፈጥፈን አንጡራ ሃብቶቹ አይደለንም፡፡ እውነቱን ለመናገር 90% ወይም ከዛ በላይ የሚሆነው የሰሜን አሜሪካ አብያተክርስያናት አማኞች በሀገር ቤት ጌታን አግኝተው በብዙ ውጣና ውረድ የጌታን ምህረትና ፊት ለምደው የመጡ ደቀ ማዘሙርት ስለሆኑ ማንም ፓስተር የድካሜ ውጤት ሊላቸው አይችልም፡፡

አማኞች ባለቤታቸው ክርስቶስ እንጂ ፓስተር ስላልሆነ ወደውና ፈቅደው ፓስተሩን በላያቸው ላይ ይሾሙታል እንጂ በግዴታ ማንም ሊሰለጥንባቸው አልተፈቀደለትም፡፡ፓስተሩም ህዝቡን ወደክርስቶስ እንዲያሳድግ ከመንጋው ባለቤት (ጌታ) አደራ ተሰጠው እንጂ ወደራሱ ሊያሳድጋቸው አይገባም፡፡ አሜሪካዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማርቲን ሉተር ኪንግ “ሰዎች ጀርባህ ላይ የሚቀመጡት ካጎነበስክላቸው ብቻ ነው” እንዳለው ምእመኑም ማንነቱንና ድርሻውን ተረድቶ ቀና ብሎ በመሄድ ከክርስቶስ ቀንበር ውጪ ሌላ ቀንበር መሸከም የለበትም፡፡ በመሰረቱ ቤተክርስቲያን የከበረችና ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰላት ቅድስተና ንጽህት ስለሆነች ማንም ፓስተር ሲፈልግ የሚከፍታትና የሚዘጋት የሰፈር ሱቅ አይደለችም፡፡

የቤተክርስቲያን ሃብት ከህግ አንጻር

እኔ በምኖርበት ሰሜን አሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት (እስቴት) ውስጥ የቤተክርስቲያን ማንነትና የንብረቷ ባለቤት ማን እንደሚሆን በተዋረድ የተሰጠ ህጋዊ መመሪያ አለ፡፡ ይህ መመሪያ የአንዱ እስቴት ከሌላው ጋር መጠነኛ ልዩነት ቢኖረውም ሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች የራሳቸው የሆነ ተመሳሳይ ህግ አላቸው፡፡ አንዲት አጥቢያ ቤተክርስቲያን የምታፈራው ሀብትና ንብረት በቤተክርስቲያኒቷ ውስጥ የሚገለገለውና የሚያገለግለው ምእመን የጋራ ንብረት እንጂ የአንድ ሰው ወይም የአንድ ወገን እንደማይሆን በህግ ተደንግጓል ፡፡ ቦሪስ ቢቲከር እና ባልደረቦቻቸው “Religion and the State in American Law[1]” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሃፋቸው በሜሪላንድና በቨርጂኒያ ለረጅም አመታት በቤተክርስቲያን ውስጥ የተነሱ በርካታ የንብረት ይገባኛል ክሶችን በመዘርዘር በሁሉም ክሶች ቤተክርስቲያንና የቤተክርስቲያን ንብረት የአባል ምእመን እንጂ የአንድ ግለሰብ ሊሆን እንደማይችል አብራርተዋል፡፡ ምንም እንኳን ህጉ አንዳንድ አሻሚና በሁለት ቡድኖች መሃከል የሚፈጠርን የይገባኛል ጥያቄ ለማስተናገድ ዝርዝር መመሪያዎች ቢኖሩትም አንድ ግለሰብ ወይም ግለሰቡን የሚወክሉ ጥቂት ሰዎች የአንድን ቤተክርስቲያን ንብረትም ሆነ ጥቅም የራሳቸው ሊያደርጉ እንደማይችሉ ያስረዳል፡፡

አንዳንድ ፍርድ ቤቶች የቤተክርስቲያንን ንብረትና ሀብት ይገባኛል የሚል አሻሚ ጥያቄ ለመመለስ በአለም የሚሰራባቸውን የግል ድርጅት መዋቅሮችንና ህጎችን ተጠቅመዋል፡፡ በዚህም አሻሚ ክስ ሲቀርብ የቤተክርስቲያኒቱ ንብረትና ሃብት ባለቤትነት የሚወሰነው ይህቺን ድርጅት (ቤተክርስቲያን) ለማንቀሳቀስ የገንዘብና የቴክንክ ድጋፍ የሚሰጠውን አካል እንደሚሆን ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ ቤተክርስቲያኒቱ ከፓስተሩ ኪስ በሚወጣ ገንዘብ የምትተዳደር ከሆነና ፓስተሩ ከምእመኑ ምንም በማይፈልግበት ሁኔታ የቤተክርስቲያኒቱ ሃብትና ንብረት የፓስተሩ ይሆናል፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ከምእመኖቿ በሚገኝ የፍቅር ስጦታ (አስራት፣ መባና የመሳሰሉት) የምትተዳደር ከሆነና ፓስተሩም የሚያገኘው ደሞዝ ከዚሁ ገቢ የተገኘ በሚሆንበት ጊዜ ቤተክርስቲያኒቱ የምእመኑ እንጂ የአንድ ግለሰብ አትሆንም፡፡ አንድ ቤተክርስቲያን ልዩነቷን ተቋቁማ መቀጠል አቅቷት በወንድሞች መሃከል መለያየት ቢፈጠር ቤተክርስቲያኒቱ ያፈራችው ሃብትና ንብረት ለሁሉም አባላት እንዲከፋፈል ህጉ ያዛል[2]፡፡ ይህንን የሚወስኑት ግን ጥቂት ግለሰቦች ሳይሆኑ የቤተክርስቲያኒቱ አባላት በሙሉ ናቸው፡፡

የቤተክርስቲያን አባላትና ግለሰቦች ከህብረታቸው ተለይተው ሌላ ህብረት በመፍጠር ሌላ ቤተክርስቲያን መመስረት ቢፈልጉ ቀድመው ከነበሩበት ቤተክስርስቲያን ያለባቸውን እዳ እንዲከፍሉና ኮንትራት ካላቸው አስቀድመው እንዲያጠሩ ህጉ ያስገድዳል፡፡ በተጨማሪም፣ አዲስ የተመሰረተው ህብረት ሃብትና ንብረት የህብረቱ አባላት ሁሉ ይሆናል እንጂ የአንድ ግለሰብ አይሆንም[3]፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃለይ የአዲስ ኪዳን አማኞች ለአንድ አላማ ተጠርተው በአንድ ላይ ሆነው የሚመሰርቱት ህብረት (ኤክሌሺያ) ቤተክርስቲያንን የፈጥራል፡፡ ሰዎችን ተጠቅሞ ቤተክርስቲያንን የሚከፍት እግዚአብሔር ብቻ ሲሆን አንድን የተከፈተች እውነተኛ ቤተክርስቲያን ደግሞ የገሃነም ደጆችም ሊዘጓት አይችሉም፡፡ ቤተክርስቲያንና እግዚአብሔር ያላቸው ህብረት በባልና ሚስት መሃከል እንዳለው ትስስር የማይበጠስ መሆኑ ቅዱስ ቃሉ ይናገራል፡፡ ማንም ሰው የሰው ሚስት ደፍሮ በሰላም እንደማይቀመጥ ሁሉ የክርስቶስ ሚስት የሆነችውንም ቤተክርስቲያን የሚደፍር መቀጣቱ አይቀርም፡፡ ከሁሉ በላይ አገልጋዮችና ፓስተሮች መረዳት ያለባቸው በቤተክርስቲያን ንብረትና ሀብት ላይ የይገባኛል ጥያቄ ማንሳታቸው ተገቢ ቢመስልም ክርስቶስ የሞተላቸውን በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉትን ምእመኖች “የኔ ንብረት ናቸው፣ ዋጋ ከፍዬባቸዋለሁ፣ ለእኔ ይገቡኛል” ብሎ ለጥያቄ ማቅረብ ግን አዕምሮን መሳት ነው፡፡ አንድ ፓስተር ቤተክርስቲያንን ሲመራ ዋጋ እንደከፈለ ቢመስለው እንኳን ዋጋውን ከቀጣሪው ከጌታ ጋር ይነጋገር እንጂ ህዝቡን የመግዘት መብት የለውም፡፡ የማንኛውም ቤተክርስቲያን ምእመኖችም እግዚአብሔር ለሾማቸው መሪዎችና አገልጋዮች በክርስቶስ ፍቅር መገዛት አስፈላጊ እንደሆነው ሁሉ የማንም ግለሰብ ባሪያ እንዳይሆኑ እንመክራለን፡፡

ዶ/ር አዳም ወንድሙ ቱሉ
Tsinat.org@gmail.com
Silver Spring, MD September, 2017
October 1, 2017

[1] U.S. Supreme Court (1970) “MD. VA. CHURCHES v. SHARPSBURG CH”. Gauge Data Solutions Pvt. Ltd. https://www.casemine.com/judgement/us/59154db8add7b06b6a7b5156. “Thus the States may adopt the approach of Watson v. Jones, 13 Wall. 679 (1872), and enforce the property decisions made within a church of congregational polity “by a majority of its members or by such other local organism as it may have instituted for the purpose of ecclesiastical government,” id., at 724, and within a church of hierarchical polity by the highest authority that has ruled on the dispute at issue, unless “express terms” in the “instrument by which the property is held” condition the property’s use or control in a specified manner.”

[2] Statute at Maryland Code Corporations & Associations Article, Section 5–209.  The statute allows that “if a charitable or religious corporation is or is about to be dissolved, or for any reason it is impracticable or inexpedient to continue the corporation’s activities, a circuit court may order the disposition of the corporate property….” https://fsb-law.com/new-maryland-case-allows-court-to-distribute-assets-of-charitable-corporation/

[3] 2010 Maryland Code CORPORATIONS AND ASSOCIATIONS TITLE 5 – SPECIAL TYPES OF CORPORATIONS Subtitle 3 – Religious Corporations

http://law.justia.com/codes/maryland/2010/corporations-and-associations/title-5/subtitle-3/5-311/

  • 5-311. Members may organize another church.

(a)  Separation and new organization.- Members of a church may separate from the church, form a house of worship, and employ a minister if:

(1) They are of sufficient number to form a house of worship and maintain a minister; and

(2) All debts and contracts incurred by them as members of the original church are discharged.  (b)  New church entitled to benefits of incorporation.- When incorporated, the new church is entitled to the benefits of this subtitle relating to religious corporations.

Click here to download the pdf: ቤተክርስቲያን የማን ናት?